Monday, February 11, 2013

የካቶሊኩ ፖፕ በዕድሜ መግፋት ከሥልጣናቸው ይለቃሉ

     

ሐራ ዘተዋሕዶ

የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ፖፕ ቤኔዲክት 16 ከሥልጣናቸው እንደሚለቁ ተገለጸ፡፡ ፖፕ ቤኔዲክት 16ከሥልጣናቸው የሚለቁት timthumb.php
 
በመጪው የካቲት 21 ቀን 2005 ዓ.ም ሲሆን በይፋ የተገለጸው ምክንያትም የዕድሜያቸው መግፋት የተደራረበ ሓላፊነታቸውን
በአግባቡ ለመወጣት ስላላስቻላቸውና በሚታይባቸው አካላዊ ድካምና አቅም ማጣት (frailty) ነው ተብሏል፡፡ የ85 ዓመት
አረጋዊው ጀርመናዊው ፖፕ ቤኔዲክት 16ኛ÷ በዓለም ዙሪያ ከአንድ ቢልዮን በላይ አማኞች ያሏትን የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ለመምራት
የተሾሙት ከስምንት ዓመት በፊት ፖፕ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊን በመተካት ነበር፡፡

 
ዘግይተው የወጡ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፣ ፖፕ ቤኔዲክት ከራሳቸው ጋራ በመምከር ከሓላፊነታቸው ለመገለል የወሰኑበትንና የቅርብ ረዳቶቻቸውን ጨምሮ ለመንግሥታትና ለበርካታ የቫቲካን ወዳጆች ድንገተኛና አስደንጋጭ በላቲን ቋንቋ የተዘጋጀ መልእክት÷ ‹‹ሦስት ቅዱሳንን ለመሠየም›› በተሰበሰበ የካርዲናሎች ጉባኤ ላይ ነበር በንባብ ያሰሙት፡፡ ከኅልፈተ ሕይወታቸው በፊት በሕመም እንደተሠቃዩት ቀደምታቸው ከአካላዊ ድካማቸው ጋራ በመንበሩ መሰንበትን ያልመረጡት ፖፕ ቤኔዲክት 16 የደረሱበት ውሳኔ ድንገተኛ ቢኾንም ‹‹ትሑት ሰብእናቸውን ያሳየ›› ነው ተብሎለታል፡፡
 
ዛሬ ከቀትር በኋላ በድንገት የተሰማውን ይህን የፖፑን ከሥልጣን የመልቀቅ ዜና ታላላቅ የዓለማችን ብዙኀን መገናኛዎች÷ ‹‹የዓመቱ የመጀመሪያ ታላቅ ሉላዊ ክሥተት›› በሚል መደነቅ እያስተጋቡት ይገኛሉ፡፡ በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ ውስጥ ያልተለመደና ከ600 ዓመታት ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ የተሰማው የፖፑ ከሥልጣን የመልቀቅ ውሳኔ÷ በፖፑ ሙሉ ፈቃድና ዕውቅና (full freedom) የተላለፈ ቢኾንም በዓለም ዙሪያ ለሚገኙት 1.1 ቢልዮን ካቶሊኮች ‹‹አስደንጋጭ ዜና ነው›› ተብሏል፡፡
 
ብዙኀን መገናኛዎቹ÷ ፖፑ በነገረ መለኰት አስተህሯቸው ቴዎሎጂያዊ ሊበራሊዝምን በማውገዝና ቅጥ የለሽ ዓለማዊነትን (aggressive secularism) በመኰነን የነበራቸውን አቋም፣ በመዋዕለ ፖፕነታቸው በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን መዋቅሮች ውስጥ ከተበራከተው ሙስና፣ የሕፃናት ጾታዊ ጥቃት፣ የፌሚኒዝም እና ሥነ ተዋልዶ አጀንዳዎች (የሴቶች ክህነት፣ ምጣኔ ውሉድ፣ ግብረ ሰዶም፣ ኤች.አይ.ቪ/ኤድስ መከላከልና መቆጣጠር) አንጻር ከሥልጣን የመልቀቃቸውን አንድምታዎችና ምልከታዎች በመተንተን ላይ ናቸው፡፡
 
በካቶሊካዊ ቀኖና ‹‹የጴጥሮስ ተተኪ›› ተብሎ በሮም መንበር የሚሾመው ፖፕ በአቅምና ጤና ማጣት ከሥልጣኑ ለመልቀቅ የሚችል ሲኾን፣ ይህም ሊፈጸም የሚችለው ፖፑ ስለሚለቅበት ምክንያት በሙሉ ፈቃዱና ነጻነቱ ሲስማማ መኾኑ ተገልጧል፡፡ ስመ ገናናውን ፖፕ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊን በመተካት በ78 ዓመት ዕድሜያቸው 265 የካቶሊክ ፖፕ ኾነው የተሾሙት ፖፕ ቤኔዲክት 16 የካቲት 21 ቀን 2005 ዓ.ም ምሽት ከሓላፊነታቸው ሲለቁ፣ በቀጣይ የሚኖረው የሽግግር ጊዜ በጣም አጭር እንደሚኾንና ተተኪው ፖፕ ከመላው ዓለም መጥተው የቆይታ ስብሰባ በሚያደርጉ ካርዲናሎች ጉባኤ (conclave of cardinals) እስከ መጋቢት መጨረሻ እንደሚመረጡ ከመንበረ ፖፑ የወጣው ዜና ያመለክታል፡፡
 
ብዙዎች ቀጣዩ ፖፕ ከጠቅላላው የካቶሊክ አማኙ ገሚሱ ሕዝብ ይገኝበታል ከሚባለውና የፕሮቴስታንታዊ የኑፋቄ ማዕበል ከሚያሰጋቸው አዳጊ አህጉር እንዲመረጥ ይሻሉ፡፡ ፖፕ ቤኔዲክት 16 ከሓላፊነታቸው እንደሚለቁ ባስታወቁበት መልእክትም ቀጣዩ ፖፕ በእጅጉ ተለዋዋጭ፣ ተለጣጭ እና ተለማጭ በኾነው ሉላዊ ኹኔታ ‹‹የጴጥሮስን ፍልኳና ታንኳ ሳያነዋውጽ›› ለመምራት የሚችል መኾን እንደሚገባው አሳስበዋል፡፡
 
እ.አ.አ በ1927 በደቡብ ጀርመን የተወለዱት ፖፕ ቤኔዲክት 16 በናዚ ጀርመን የሂትለር ወጣቶች ውትድርና የአየር መቃወሚያ ምድብ በመኾን በውጊያ ተሳትፈዋል፡፡ ምሁራዊነታቸው የሚታወስበትን ፍልስፍና እና ቴዎሎጂን ያጠኑ ሲኾን ለፖፕነት ከመመረጣቸው በፊት የሙኒክ ሊቀ ጳጳስ/ካርዲናል በመኾኑ ሠርተዋል፤ ለኻያ ዓመታት የፖፕ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ የቅርብ ረዳት በመኾን አገልግለዋል፡፡
 
ንጽጽርም ውድድርም የማይቻልና የማይገባ ቢኾንም በቤታችንም÷ ፓትርያሪኩ በሕይወት ሳለ በራሱ ፈቃድ፣ በሕመም ወይም በዕርግና ሓላፊነቱን ለመወጣት የማይችልበት ኹኔታ ሲያጋጥም ከመንበሩ ከሥልጣን የመገለሉ ጉዳይ በአዲስ በተዘጋጀው የፓትርያሪክ ምርጫ ሕግ አከራካሪ እንደኾነ ጸድቋል፡፡ ከዚህም በተለየ መልኩ የተሿሚው ዘመነ ፕትርክና በተወሰነ ዓመት እንዲገደብ ያሰቡም አልጠፉ፡፡

No comments:

Post a Comment