Saturday, January 19, 2013

በምርጫው ባለመሳተፋችን ኢሕአዴግና መንግሥት ይከስራሉ››

‹‹በምርጫው ባለመሳተፋችን ኢሕአዴግና መንግሥት ይከስራሉ››
20 January 2013 ተጻፈ በ

‹‹በምርጫው ባለመሳተፋችን ኢሕአዴግና መንግሥት ይከስራሉ››

አቶ አስራት ጣሴ፣ የ33 ተቃዋሚ ፓርቲዎች የጋራ ኮሚቴ ሰብሳቢ

አቶ አስራት ጣሴ የመድረክ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል ናቸው፡፡ በአሁኑ ወቅት ደግሞ በ33 ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች የተመሠረተው የጋራ ኮሚቴ ሰብሳቢ ናቸው፡፡
ኮሚቴው ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፣ ለኢሕአዴግና ለመንግሥት 18 ነጥቦች በማንሳት በሚያዚያ ወር በሚካሄደው የአካባቢና የአዲስ አበባ ከተማ ምርጫ ከመከናወኑ በፊት ድርድር እንዲደረግ ጠይቆ ነበር፡፡

ምርጫ ቦርድም ኢሕአዴግም ፈቃደኞች ሳይሆኑ ቀርተው ጥያቄያቸውን ውድቅ አድርገውባቸዋል፡፡ የምርጫ ምልክት የሚወሰድበት የጊዜ ሰሌዳም አልፏል፡፡ ፓርቲዎቹ ግን ሕዝባዊ ስብሰባ በመጥራት በገዥው ፓርቲ ላይ ጫና ለመፍጠር ማቀዳቸውን ይናገራሉ፡፡ በምርጫውና በፓርቲዎቹ አንቅስቃሴ ላይ የማነ ናግሽ አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- በአንድ በኩል እናንተ ከምርጫ ውጭ አይደለንም እያላችሁ ነው፡፡ በሌላ በኩል ምርጫ ቦርድ ባወጣው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት የምርጫ ምልክት የሚወሰድበት ጊዜ ተጠናቆ ወደ ሕትመት ተገብቷል፡፡ ራሳችንን ከሒደቱ አላገለልንም የምትሉትና በተግባር እየሆነ ያለው እንዴት ይጣጣማል?

አቶ አስራት፡- እኛ ስለ ምርጫ ስናስብ ምርጫን ለብቻው ነጥለን አናስበውም፡፡ ከመላው የአገራችን ፖለቲካ ተነጥሎ የሚታይ አይደለም፡፡ ስለዚህ በምርጫው ምክንያት ለጠየቅናቸው 18 ጥያቄዎች ከምርጫ ቦርድ፣ ከኢሕአዴግና ከመንግሥት ጋር መደራደሩ ከምርጫም በላይ ስለሚሆን አገራዊ ጠቀሜታ አለው ብለን እናምናለን፡፡ በተቃዋሚዎችና በመንግሥት መካከል ድርድር ቢጀመር፣ ብሔራዊ የመግባቢያ ፎረም (መድረክ) ቢፈጠር ከምርጫም ባሻገር ላሉ አገራዊ የፖለቲካ፣ የሕግ የበላይነት፣ የዲሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብቶች የሙስና የመልካም አስተዳደር እጦትና ሌሎች ጉዳዮችን መነጋገርና መወያየት ለአገር ሰላምና መረጋጋት፣ ለሕዝቦች ሰላም ለአገር አንድነትና ልማት ልዩ ልዩ ጠቀሜታ አለው፡፡ ከምርጫ ወጥተናል ብሎ በአራት ነጥብ መዝጋት ኃላፊነትን በትክክል እንደተወጣን አንቆጥረውም፡፡ ለዚህም ነው ቢረፍድም ነገ ከነገ ወዲያ የመነጋገር አጀንዳ ከተከፈተ ሁልጊዜም የጊዜ ሰሌዳ ሊጠብም ሊሰፋም የሚችል ነው፡፡ የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል አይደለም፡፡ ስለዚህ ማስታመም ያስፈልገል፤ የምናስታምመው ደግሞ ለአገርና ለሕዝብ ስለሆነ ነው፡፡ በምርጫ ቦርድ ሕግና ደንብ መሠረት ቴክኒካሊ ወጥተናል፤ አስወጥተውናል፡፡ ነገር ግን ምርጫ ቦርድ ኃላፊነቱን እየተወጣ አይደለም፡፡ የተለያዩ ማስረጃዎችን ማቅረብ ይቻላል፡፡

አንድ ምሳሌ ልጥቀስልህ፡፡ የምርጫ አንድ ትልቅ ነገር የመራጮች ሚስጥራዊነት ነው፡፡ ነገር ግን በ2002 ምርጫ አንድ ለአምስት ተደራጅተው ሲመርጡ አይተናል፡፡ ዜጎች የመምረጥም ያለመምረጥም መብታቸው በሕግ የተጠበቀ ነው፡፡ ነገር ግን ሰዎች ወጥተው እንዲመርጡ እየተገደዱ ነው፡፡ ምርጫ ቦርድ ይኼን ሁሉ የሕግ ጥሰት ሰምቶ እንዳልሰማ ቁጭ ብሎ እያየ ነው፡፡ ስለዚህ ኃላፊነቱን እየተወጣ አይደለም፡፡ ወደ ጥያቄው ለመመለስ አሁንም ምንም ቢዘገይም፣ መንግሥትም ምርጫ ቦርድም ኃላፊነት ተሰምቷቸው አገራዊና ሕዝባዊ መግባባት እንዲፈጠር ያቀረብናቸውን ጥያቄዎች በሰከነ አዕምሮ እንዲፈትሹ እንጠይቃለን፡፡

ሪፖርተር፡- አብዛኛዎቹ ጥያቄዎች አጠቃላይ የአገሪቱን የፖለቲካ ሁኔታ የሚዳስሱ ናቸው፡፡ ከዚህ በፊትም ሲነሱ የቆዩ ችግሮች ናቸው፡፡ አሁን በዘንድሮ የምርጫ ሒደት የተከሰቱ አዲስ ክስተቶች አይደሉም፡፡ ምናልባት እንነጋገር የምርጫ ሜዳው ይስተካከል ማለት ተገቢ ነው፡፡ ነገር ግን ገና ለገና ሒደቱ ምን እንደሚሆን ሳታዩ ራሳችሁን ከሒደቱ (ቴክኒካሊ) ውጭ ማድረግ አግባብ ነው ይላሉ? ሒደቱ ውስጥ ሆናችሁ ጥያቄያችሁን ማንሳት አትችሉም ነበር?

አቶ አስራት፡- ከተጨባጭ ሁኔታ ተነስተን ነው ጥያቄያችንን እያቀረብን ያለነው፡፡ በምርጫ 2002 የሆነውን ታውቀዋለህ፡፡ 99.6 በመቶ የሚባል የፓርላማ ወንበር ማግኘት በየትኛውም የዲሞክራሲያዊ ሥርዓት የሚመራ አገር ታሪክ አታገኘውም፡፡ በዚያን ጊዜ የነበሩ ችግሮች ተጠናክረው ቀጥለዋል፡፡ ስለዚህ ለይስሙላ በሒደቱ መሳተፍ ኢሕአዴግን ከማጀብ ውጪ ምንም ውጤት የለውም፡፡ አንድ ሰው አንድ ጊዜ ካታለለህ ነውሩ የአታላዩ ነው፡፡ ለሁለተኛ ጊዜ ካታለለህ ግን ነውሩ የተታላዩ ነው የሚሆነው፡፡ ምክንያቱም የ2002 ምርጫ ስህተት ከአሁኑ ይታረም ተብሎ አሁን ጥያቄ ይቀርባል፡፡ በ2005 ምርጫ ተመሳሳይ ስህተት እንዳይደገም ይደረጋል፡፡ ምርጫ ደግሞ ቀላል ነገር አይደለም፡፡ ወሳኝ ነገር ነው፡፡ በመድብለ ፓርቲ ሥርዓት ወደ ሥልጣን መውጫ አንድ ብቸኛ መንገድ ነው፡፡ ሕዝቡ ደግሞ አልተመቸኝም አልሆነልኝም የሚለውን መንግሥት ከሥልጣን የሚያወርድበት፣ ይሠሩልኛል ብሎ የሚያስባቸውን ወደ ሥልጣን የሚያወጣበት መንገድ ነው፡፡ እንዲያው እርስዎም ይሞክሩት የሚባል ጨዋታ አይደለም፡፡ ለዛሬ አልተሳካልዎትም፣ እንደገና ዕድልዎን ይሞክሩ ቀልድ ነው የሚሆነው፡፡

ሁለት ምሳሌዎችን ላንሳ፡፡ አንዱ የመንግሥት ሚዲያ ከገዥው ፓርቲ ተፅዕኖ ተላቆ ገለልተኝነቱ ስለሚረጋገጥበትና ተቃዋሚ ፓርቲዎች ሽፋን ስለሚያገኙበት ነው፡፡ ይኼ ደግሞ ከ2002 ምርጫ ጀምሮ በየጊዜው በምንሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ለሁለት ሰዓታት ያህል ሲቀርፁ ቆይተው አንድ ደቂቃም አያቀርቡልንም፡፡ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ለሰከንዶች ፎቶግራፍ አሳይተው ከአጀንዳችን ውጪ ያቀርቡናል፤ ይኼ ታክስ በሚከፍለው ሕዝብ ገንዘብ በሚተዳደር ሚዲያ መቀለድ ነው፡፡ ይህንን በ2002 ምርጫ አይተነዋል፡፡

ሁለተኛ የአንድነት ልሳንን ተመልክት፡፡ አንድ ልሳን ለአንድ የፖለቲካ ፓርቲ ወደ ሕዝብ የሚገባበት፣ ፕሮግራሙንና የፖሊሲ አማራጩን ለሕዝብ የሚያቀርብበት፣ ሕዝብን የሚያደራጅበት፣ ከሕዝብ ደግሞ ምን ማድረግ እንዳለበት መልሶ የሚማርበት መሣርያ ነው፡፡ ይኼንን በጠራራ ፀሐይ ነው የተነጠቅነው፡፡ በመጀመርያ ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት አላታምም አለ፡፡ ቀጥሎ ወደ ግል አሳታሚ ስንሄድ የጋዜጣውን አድራሻ ካዩ በኋላ እንዳይታተም ይከለክሉናል፡፡ አንዳንዶቹ ቀብድ ከወሰዱ በኋላ፣ ገንዘባችሁን ውሰዱ ብለው የመለሱልን አሉ፡፡ ማስረጃዎች በእጃችን አሉ፡፡

ሌላ ደግሞ አሁን በቅርቡ በሚኒስትር ማዕረግ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ሙክታር ከድር የመንግሥት ሠራተኛ አንድ ለአምስት መደራጀት አለበት ብለዋል፡፡ እንደዚህ የሚባል አደረጃጀት ደግሞ በሲቪል ሰርቪሱ ውስጥ የለም፡፡ በመንግሥት መሥርያ ቤቶች እንደ ሥራ አመቺነቱ እንደ ራዕዩ የራሱ መዋቅር አለው፡፡ አሁን አንድ ለአምስት እንዴት ነው የሚዋቀረው? ማንና ማንን ነው በአንድ ለአምስት የሚዋቀረው? በዚያ ውስጥ ደግሞ ሦስት ክንፍ አለው ይላል፡፡ የመንግሥት፣ የኢሕአዴግና የኅብረተሰብ ክንፍ፡፡ እንዲህ ዓይነት አደረጃጀት የፖለቲካ ሥራ የሚሠራበት እንጂ ከዚያ ውጭ የሚሆን አይደለም፡፡

ሪፖርተር፡- ኢሕአዴግ እንደ ገዥ ፓርቲ ፖሊሲውን እያስፈጸመ ስለሆነ ማናቸውንም ዓይነት አደረጃጀት ተጠቅሞ ልማት ቢያፋጥን ምን ችግር አለው? ዋናው ቁም ነገር በዚህ አደረጃጀት ሰዎች ተገደው የሚገቡበት አለመሆኑ ነው፡፡

አቶ አስራት፡- እኛ ደግሞ ተገዶ የሚደራጅበት ነው የምንለው፡፡ በመጀመሪያ ደግሞ በመርህ ደረጃ ፓርቲዎች በመንግሥት መዋቅር ውስጥ አይገቡም፡፡ በበጎ ፈቃደኝነት አይደለም፡፡ ኢሕአዴግ በመንግሥት መሥርያ ቤት ውስጥ ትልቅ ዱላ አለው፡፡ አንዱ ዕድገት ነው፡፡ ሠራተኛው የሚያድገው፣ የሚሾመው፣ የሥልጠናና የትምህርት ዕድል የሚያገኘው ከኢሕአዴግ ጋር ባለው ግንኙነት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ቅድም እንዳነሳነው አሁን የተነሱት 18 ጥያቄዎች ከዚህ ቀደም በተለይ ከምርጫ 2002 በኋላ ሲነሱ የቆዩ ናቸው፡፡ አሁን ምርጫ ሲቃረብ በአጋጣሚ ምርጫ ቦርድ በጠራው የአዳማ ስብሰባ ተገናኝታችሁ ከምትሰባሰቡ፣ ቀደም ብላችሁ እንዲህ ዓይነት መሰባሰብ በመፍጠር ጫና ማድረግ አትችሉም ነበር ወይ?

አቶ አስራት፡- ጥያቄው ተገቢ ነው፡፡ ግን ከሁለት አቅጣጫ ልመልሰው፡፡ የጥቅምት 15 ቀን 2005 ዓ.ም. የአዳማ ስብሰባ የመጨረሻ ውጤት እንጂ የመጀመርያ ውጤት አልነበረም፡፡ ከዚያ በፊት የተጀመረ ነበር፡፡ አንደኛው መድረክ እንደ ፓርቲ ከመኢአድና ከሰማያዊ ፓርቲ ጋር ተደጋጋሚ ውይይት አካሂዷል፡፡ ለዚያውም በሊቀመንበርነት ደረጃ እስከ መግባቢያ ሰነድ ማዘጋጀት ተደርሶ ነበር፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ አንድነት ለብቻው ከሌሎች አሥራ አንድ ፓርቲዎች ጋራ የብዙ ወራት ድርድር አድርጓል፡፡ እነዚህ ድርድሮች ናቸው አዳማ ላይ አመቺ ሁኔታ የፈጠሩት፡፡ ነገር ግን በአንድ ቀን አይታሰብም ነበር፡፡ ቀደም ብሎ የተሠራ ነው፡፡ በመንግሥትም ደረጃ ከመድረክ የእንደራደር ጥያቄ በተከታታይ ይቀርብ ነበር፡፡ አንድ እንቅፋት ሆኖ የቆየው በኢሕአዴግ በኩል የሚቀርበው የምርጫ ሥነ ምግባር አዋጁን ፈርሙ የሚል ነው፡፡ ያንን የማናደርግበትን ምክንያት ደግሞ ከበቂ በላይ ደጋግመን አስረድተናል፡፡

ሪፖርተር፡- ያም ሆኖ የምርጫ ምልክቱን ወስዳችሁ እስከ መጨረሻ ማየት አልነበረባችሁም ወይ?

አቶ አስራት፡- ይህ ከባድ ጥያቄ ነው፡፡ የስልት ጥያቄ ነው፡፡ እንዳልከው የምርጫ ምልክት ተወስዶ ወደ መጨረሻ ደረጃ ሲደርስና ሁኔታዎች አላሠራም ሲሉ መውጣት አንዱ ስልት ነው፡፡ ሌላው ስልት እኛ የመረጥነውን ነው፡፡ ይህንን የመረጥንበት ምክንያት ደግሞ ከኢሕአዴግ ባህሪ ስንነሳ ጥያቄ አቅርበን እንደዚህ ጥያቄያችን በተወረወረበትና ጆሮ ዳባ ልበስ በተባለበት ሁኔታ ተመዝግበን የምርጫ ምልክት ወስደን አብረን መንከባለል ከሕዝብ የሚነጥል ነው፡፡ የፖለቲካ ኪሳራም ያስከትላል፡፡ ኢሕአዴግ አገራዊ ኃላፊነት ተሰምቶት ጥያቄያችን ባልመለሰበትና ‹‹ውሾች ይጮኻሉ ግመል ጉዞውን ቀጥሏል›› በሚልበት ሁኔታ ምርጫ ውስጥ መግባት ተገቢና ትክክል አይደለም በሚል እምነት እንደ ስልት የበለጠ ጉልበት አግኝተንበታል፡፡

ሪፖርተር፡- አሁን ኢሕአዴግም ምርጫ ቦርድም ተገደው ወደ ድርድር እንዲመጡ በማለት ሕዝባዊ ስብሰባዎች ለመጥራት አቅዳችኋል፡፡ ምን ያህል ጫና እንፈጥራለን ብላችሁ ታምናላችሁ? ከኢሕአዴግ የፖለቲካ ባህሪ አንፃር ምን ዓይነት ውጤት ያስገኛል የሚል እምነት አለዎት?


አቶ አስራት፡- እንዲህ በቀላሉ የሚመለስ ጥያቄ አይደለም፡፡ ከባድ ጥያቄ ነው፡፡ ቀላል መልስም የለውም፡፡ ግን ሌላም አማራጭ የለውም፡፡ ለ33ቱም ሆነ ለሌሎች ተቃዋሚዎች ሌላም አማራጭ የለም፡፡ አማራጩ ሰላማዊ ትግሉን ወደፊት ማራመድ ብቻ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ የሕዝብ ድጋፍን ማሰባሰብ ያስፈልጋል፡፡ የሕዝብ ድጋፍ ደግሞ አለ፡፡ በ2002 ምርጫም አይተናል፤ አሁንም በተለያዩ መንገዶች አይተናል፡፡ ኢሕአዴግ ከምርጫ 97 ጀምሮ የሕዝብ ድጋፍ እንደሌለው ካወቀ በኋላ፣ ጠቅላላውን የፖለቲካ ምኅዳር ከማጥበብ ወደ ማዳፈን ነው የሄደው፡፡ ይኼ የፍርኃት ምልክት ነው፡፡ በሕዝብ ያለመተማመን ምልክት ነው፡፡ ሕዝብ ይመርጠኛል፣ ትክክለኛ ሥራ ሠርቼያለሁ ለሚል መንግሥት አንድ ለአምስት ሕዝብን መጠርነፍ አስፈላጊ አይደለም፡፡ እቤት ለቤት እየሄደ ካልተመዘገባችሁ እያለ ማስገደድም አያስፈልገውም፡፡


ሪፖርተር፡- ሕዝቡ ወጥቶ በምርጫ እንዲሳተፍ መቀስቀስ ምን ክፋት አለው?

አቶ አስራት፡- መቀስቀስ አይደለም የምልህ፣ ካርድ ውሰዱ ብሎ ማስገደድ ነው፡፡ አዋጁ አይፈቅድም፡፡ አንድ ሰው የመምረጥም ያለመምረጥም ሕገ መንግሥታዊ መብት አለው፡፡ የሕዝቡ ፈቃድ የለም፤ ተመዝጋቢ መራጭ የለም ከሚል ሒሳብ የሚመጣ ነው፡፡ ያለበለዚያ ነፃ ፕሬስንና የፖለቲካ ፓርቲዎችን ልሳን ማፈን አያስፈልገውም’ኮ፡፡ በሕዝብ ተቀባይነት ያለው መንግሥት የሚያሰጋው ነገር የለም፡፡ እኛ ግን የምናውቀው ሕዝቡ ዛሬ በመልካም አስተዳደር እጦት መከራውን እየባላ ነው፡፡ ዛሬ ሕዝብ በኑሮ ውድነት እየተሰቃየ ነው፡፡ ሕዝብ ዛሬ ፍትሕ እያገኘ አይደለም፡፡ የሕዝበ ሙስሊሙ ጥያቄ እንኳን እንደ አንድ ምሳሌ ሊወሰድ ይችላል፡፡ መንግሥት በሃይማኖት ጣልቃ ገብቶ የሙስሊሙን ማኅበረሰብ እያስቸገረ ነው፡፡ ከዚያም በኩል ድጋፍ የለኝም የሚል ሙሉ ለሙሉ ሥጋት አለው፡፡ በነጋዴዎች በኩል በፈቃድ ማደስ ጫና ራሱ አጥንቶ የደረሰበት ጉዳይ ነው፤ ተቀባይነት የለውም፡፡ በመምህራን ደመወዝ ጭማሪ ምክንያት ያኮረፈው ይበዛል፡፡ አሁን በተነሳው ጉዳይ ሕዝቡ እኛን ተከትሎ እንደሚመጣ እርግጠኛ ነኝ፡፡ ነገር ግን ምን ያጋጥማል? ምን ዓይነት ሁኔታ ይፈጠራል? ፈቃዱ ይገኛል? ካልተገኘ ምንድን ነው የሚደረገው? በሒደት ውስጥ የምናየው ይሆናል፡፡ በእኔ እምነት ግን ሕዝብን ማነቃነቅ እንችላለን፡፡ ውጤትም እናመጣለን፡፡ ይኼንን ሰላማዊና ሕጋዊ ትግል በኃይል ልጨፍልቅ ቢል የሚከተለው ችግርና አበሳ ለሕዝብም ለአገርም አያመችም፡፡ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆን ኦፍ ኬኔዲ የተናገሩት ልጥቀስልህ፣ ‹‹A government that really makes peaceful revolution impossible will make violent revolution inevitable.›› [ሰላማዊ ትግልን የማይቻል የሚያደርግ መንግሥት የአመፅ አብዮት እንዲመጣ ያስገድዳል]፡፡ ይኼ ደግሞ እኛ የምንፈልገው አይደለም፡፡

ሪፖርተር፡- ሕዝቡ በፖለቲካው መስክ ተስፋ የቆረጠ ወይም የተሰላቸ ይመስላል፡፡ በእንዲህ ዓይነት ሁኔታ ሕዝባዊ ስብሰባ መጥራት ውጤት ይኖረዋል? ከምርጫው ሒደት ውጭ ብትሆኑስ ማነው የሚጠቀመው?

አቶ አስራት፡- በዚህ ምርጫ ባለመሳተፋችን ኢሕአዴግና መንግሥት ይከስራሉ ብዬ ነው የማምነው፡፡ አንደኛ 33 ፓርቲዎች ሳይሳተፉ አሸነፍኩ ቢል ተቀባይነቱና ሕጋዊነቱ ጥያቄ ውስጥ ይገባል፡፡ ሁለተኛው ለኢትዮጵያ ሕዝብም ቢሆን ፓርቲዎች ሥልጣን በሰላማዊ መንገድ ይለዋወጣሉ የሚለውን ዕድል ያሳንሰዋል፤ ያደበዝዛል፡፡ ያ ማለት ወዳልተፈለገ አዙሪት የሚወስድ ነው፡፡ ኢሕአዴግ ወደ ሥልጣን ወደ መጣበት አዙሪት ይሄዳል፡፡ ይኼ ደግሞ ለራሱም፣ ለአገርም ጥፋት ነው፡፡ ይህ ካላሰጋው ማን ሊያሰጋው ነው? አንድ የሕወሓት ወታደር ለመጀመርያ ጊዜ በሬዲዮ ሲናገር ‹‹ብሶት የወለደው…›› ሲል ተሰምቷል፡፡ እነሱን ብሶት ከወለዳቸው ሌሎች ብሶት የሚወልዳቸው አይፈጠሩም? ይህንን አለማሰብ ከዓለም ታሪክና ከራስ ታሪክም አለመማር ነው፡፡ በጉልበት በማሰርና በመግደል የተወሰነ ጊዜ ይኬዳል እንጂ እስከ መጨረሻ ውጤታማ መሆን አይቻልም፡፡ አንድ ባልከው ሐሳብ እስማማለሁ፡፡ ሕዝቡ ተሰላችቷል፣ ፍርኃትም ሰፍኗል፡፡ ይኼ ሁሉ ኢሕአዴግ የፈጠረው ነው፡፡ ይኼ በፍርኃት ጠፍንጎ መያዝ አንድ ቦታ ላይ ይቆማል፡፡ የታሪክ ሀቅ ነው፡፡ ፍርኃት ይጠራቀም ይጠራቀምና አንድ ቦታ ላይ ይፈነዳል፡


ሪፖርተር፡- መድረክ ከኢሕአዴግ ጋር ባለው ቁርሾ ምክንያት ለማጥላላትና ተቀባይነት ለማሳጣት 33 ፓርቲዎችን አሰባስቦ በእነሱ ሽፋን የራሱን አጀንዳ እያካሄደ ነው ይባላል፡፡


አቶ አስራት፡- ኢሕአዴግ ይህንን ቢል አይገርመኝም፡፡ ነገር ግን እውነቱ ያ አይደለም፡፡ አንደኛ መድረክ ከኢሕአዴግ ጋር ለመደራደር የጻፋቸው ደብዳቤዎች ብዙ ናቸው፤ አንተም ታውቃቸዋለህ፡፡ ድርድሩም ተጀምሮ ከዚያ የወጣንበት ምክንያት ‹‹እንዳያማህ ጥራው እንዳይበላ ገፍትረው›› ሥርዓት ስለሚጠቀም፣ እንደ እኩል ፓርቲ ሳይሆን በእኔ መንገድ ካልሄዳችሁ መጨረሻችሁ እስር ቤት ነው ወይ መባረር ነው እያለ ነው እንጂ እኛ ከኢሕአዴግ ጋር ጠላትነት የለንም፡፡ ከመፈራረጅ ፖለቲካ እንዲወጣ ነው የምንፈልገው፡፡ እሱ ነው በጠላትነት የሚያየን፤ በፀረ ሰላም ስለሚፈርጀን የእሱ ነፀብራቅ ነው የሚከሰን፡፡ እኛ ከመንግሥትም በላይ የዚህ አገር ደኅንነትና ህልውና የሚያሰጋን ሰዎች ነን፡፡ ያለዚያማ ሌላ አማራጭ’ኮ ኢሕአዴግ አይደለም የሚሰጠን፡፡


የትግል ስልት ማንም አይመርጥልንም፡፡ አንዴ የሻዕቢያ ተላላኪ፣ ሌላ ጊዜ የፀረ ሰላም ቡድኖች ጉዳይ አስፈጻሚ እያለ የሚከሰን እሱ ነው፡፡ እኛ ያ አይደለንም፡፡ እንዲያ እያለ ከኦብነግ ጋር እየተደራደረ አይደለም እንዴ? እዚህ በአገራችን ቁጭ ያልን ሰዎችን የምርጫ ሥነ ምግባር አዋጁን ካልፈረማችሁ አንደራደርም እያሉ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ግን አስመራ ድረስ ሄደው ለመደራደር ፈቃደኛ ነኝ ብለዋል፡፡

 

No comments:

Post a Comment