Tuesday, January 22, 2013

የኤርትራ መንግስት አደጋ ላይ ወድቋል

Presidant Isaias Afewerki ፕሬዝዳንት ኢሣያስ አፈወርቂ
PrintE-mail
የፕ/ት ኢሣያስ አፈወርቂ ሴት ልጅም ታግዳለች
በአገዛዙ የተማረሩ ወታደሮች የቴሌቭዥን ጣቢያውን ተቆጣጥረውት ነበር
 
 (ማክሰኞ ጥር 14 ቀን 2005 ዓ.ም. January 22, 2013)፦ ከሁለት መቶ በላይ የሆኑ የኤርትራ መንግስት ወታደሮች መንግስታቸውን ተቃውመው በትናንትናው ዕለት ሰኞ ጀንዋሪ 21/2013 ዓ.ም. የማስታወቂያ ሚንስቴሩን መ/ቤት ከበው በቁጥጥር ስር አውለዋል። የፖለቲካ ተሀድሶ እንዲደረግና የህሊና እስረኞች በሙሉ እንዲፈቱ ሀሳብ እንዳላቸውም አስታውቀዋል።
ይህንን ሃሳባቸውን የተናገሩት የዜና ማሰራጫውን ጽ/ቤቱን ሰራተኞች አስገድደው በማስነበብ ሲሆን፣ ከዛን ጊዜ በኋላ የቴሊቪዥንም ሆነ የሬድዮ ስርጭቱ እንደተቋረጠ ታውቋል። መ/ቤቱን የተቆጣጠሩት ወታደሮች ወጣቶች ሲሆኑ፣ ቁጥራቸው መቶ እንደሚሆን ታውቋል። እነዚህ በተለይም በፕሬዝዳንት ኢሣያስ አፈወርቂ አገዛዝ የተማረሩት ወጣት ወታደሮች በተቆጣጠሩት ማስታወቂያ ሚኒስቴር መስሪያ ውስጥ አግተዋቸው የነበሩትን ሴቶችና ሕፃናት ለቅቀዋቸዋል።
ከታጋቾቹ ውስጥ የፕሬዝዳንት ኢሣያስ ሴት ልጅ እንደምትገኝበት የኤርትራውያን ድረገጾች ዘግበዋል። የተለቀቁት ሰዎች ወጣቶቹ ወታደሮች ትሁቶች መሆናቸውንና የበላይ አለቆቻቸው ምንም በሀገሪቱ የተሻለ ለውጥ እንዲመጣ ባለማድረጋቸው የተበሳጩ መሆናቸውን ገልፀዋል።
በትናንትናው ዕለት የፕሬዝዳንቱ ጽ/ቤት እና የአስመራ አውሮፕላን ማረፊያ በታንክና በወታደሮች ተከብቦ የነበረ ሲሆን፣ ወታደሮቹ የወጣቶቹ ደጋፊዎች ይሁኑ የፕሬዝዳንቱ ታማኞች ለማወቅ አልተቻለም። የበላይ መኮንኖች በጉዳዩ ጣልቃ ለመግባት ፍላጎት እንዳልነበራቸው ታውቋል።
በአሁኑ ጊዜ ከተማውን ማን በበላይነት እንደሚመራ መታወቅ ያልተቻለ ሲሆን፣ በአንጻሩ የተኩስ ልውውጥም ሆነ የጥይት ድምጽ እስከ ትናንትናው ምሽት ድረስ አልተሰማም። አስመራ ከወትሮው የተለየ ወታደራዊ እንቅስቃሴ ይታይባታል የሚሉ የውጪ ሀገር የኢንባሲ ሰራተኞች ሲኖሩ፤ በነዋሪው በኩል የሚታየው ሁኔታ ግን ከወትሮው የተለየ እንዳልሆነ የሚገልጹ አሉ።
የአሜሪካ ሬድዮ የአማርኛው ክፍል በትናንትናው ምሽት የዜና እወጃው ተቃዋሚዎቹ በ1997 ዓ.ም. የወጣው ሕግ እንዲከበር፣ የፖለቲካ እስረኞችም እንዲፈቱ የሚገልጽ ዜና ማስተላለፋቸውን ገልጾ፤ የተቃዋሚዎቹ ዓላማ ምን እንደሆነ ከሌሎች የዜና ማሰራጫዎች ወይም ከአስመራ የተሰማ ዜና እንደሌለ አስታውቋል።
ተቃዋሚዎቹ የማስታወቂያ ሚንስቴሩን ጽ/ቤት ብቻ ሳይሆን ሌሎችንም የመንግስት ተቋማት ለመቆጣጠር ሙከራ ለማድረጋቸው ፍንጭ ቢኖርም፤ ዓላማቸው በግልጽ ሊታወቅ እንዳልቻለ በተጨማሪ የገለጸው የአሜሪካ ሬድዮ፤ የአስመራ መንግስት እራሱን አግልሎ የሚኖር ከመሆኑም በላይ የሱማሌ ሽምቅ ተዋጊዎችን በገንዘብና በመሳሪያ ይደግፋል በመባሉ ከሦስት ዓመት በፊት የተባበሩት መንግስታት ጽ/ቤት እቀባ እንዳደረገበት አስታውሷል።
በትናንትናው ዕለት በኤርትራ የሞባይል ስልኮች ይሰሩ የነበሩ ቢሆንም ኢንተርኔት ግን ከአግልግሎት ውጭ እንደነበር ለማወቅ ተችሏል። ኢንተርኔት የተቋረጠበት ምክንያት በሰርቨር መጨናነቅ ይሁን፣ ይህንን የለውጥ እንቅስቃሴ ለመግታ በተደረገ ሙከራ በትክክል ለማወቅ አልተቻለም።

No comments:

Post a Comment