Saturday, January 19, 2013

ምን ይሆን ሚሰጥሩ ስንጥቅ የሚያረገኝ?

    
ምን ይሆን ሚሰጥሩ ስንጥቅ የሚያረገኝ፡
ምን ይሆን ሚሰጥሩ ስንጥቅ የሚያረገኝ?

ቀስተ ደመና ሳይ ልቤን እሚርድብኝ?
ጨርቃችሁ ይውለብለብ ከወደዳችሁት ሲባል የነበረ፤
ለአንባሻ ማስጫ ሆኖ የተወጠረ፡
ደቡብ አፍሪካ ላይ ገነነ ከበረ።

አረንጓዴ ብጫ ቀዩ ሰንደቃችን፡
የበርሊን ታዳሚን ማሸማቀቂያችን።
በባንዳ ተቀዶ ሲደራረት ኖሮ፡
ዳግም ተወለደ ታየኝ ዛሬም አምሮ።
ምስጋና ለናንተ ጫፉን ለያዛችሁ፡
ለመናኛ ባንዳ መርዶ ያረዳችሁ፡
ሊሰቀል ሲዘጋጅ ጣረሞት ጥብቆ፡
ጀግናው ተሰለፈ በባንዲራው ደምቆ፡
ሞቶ ይሁን ተኖ ቅጡ ላልታወቀ የባንዳ አለቃ፡
ለምንስ ማቅ ትልበስ የደቡብ አፍሪቃ?
የማንዴላ አገር የነጻነት ጮራ፡
የጣረሞት ሳይሆን አንበሳው ያጓራ፡
ምንጊዜም ላርማዬ፤ ምን ጊዜም ላገሬ፡
በስደት፤ በስቃይ አይቀዘቅዝ ፍቅሬ፡
ብላችሁ
ተጎናጽፋችሁ ሳይ የክብር መንጦልያ፡
ምንም ብትከሺ አትጠፊም ኢትዮጵያ።
የሚለው ተስፋዬ ዳግም ለመለመ፡
የወያኔ ጫጉላ በቃው አከተመ።
 
እግዝአብሄር ኢትዮጵያን ይጠብቅ
እስከ ነጻነት
በደቡብ አፍሪቃ ተሰደው ለምገኙና ንጹሁን የኢትዮጵያ ባንዲራ ከፍ አርገው ላገነኑ ላውለበለቡ ጅግኖች
መታሰቢያ ትሁንልኝ

No comments:

Post a Comment